Category: Social

ከ21 ዓመት በኋላ (ዴሞክራሲ ሲሰላ)

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ 'በ' - ጉብጠትኢሕአዴግ ከ21 ዓመታት በኋላ በዴሞክራሲ ጎዳና ወደኋለ መመለሱን ለማረጋገጥ ጥናት አያስፈልገውም፡፡ ታሪክን ባጭሩ ‹‹መገረብ›› በቂ ነው፡፡ ሆኖም ከሰሞኑ የተሰራች ትንሽዬ ቅኝትም የምንገርበውን የታሪኩን ወቅታዊ ደረጃ ውጤት ታረዳናለች፡፡

ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግል አምባገነኑን ደርግ ከገረሠሠ በኋላ የሽግግር መንግስት አቋቋመ፡፡ የሽግግር መንግስቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ በነፃ ሐሳብ የመግለፅ መብትን እና ወዘተ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚደነግገውን ሕገ መንግስት ቀረፀ፡፡

በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ምርጫም (ከነእንከኑ) ተካሄደ፣ ተደገመ፡፡ በርካታ የግል ጋዜጦች ተከፈቱ፣ ብዙ ሰዎችም ትንፋሽ ታፍኖ ከሚኖርበት የደርግ የኑሮ ዘዬ በከፊል በመላቀቅ ለመብታቸው ጥብቅና መቆም እና ሐሳባቸውን መግለፅ ጀመሩ፡፡ በዚህ መሃል ሦስተኛው ብሔራዊ ምርጫ (97) መጣ፡፡ ያ ወቅት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከፍተኛ ጫፍ (maximum peak) ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር፡፡

ምርጫ 97 መጨረሻው ብጥብጥ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ እያቆጠቆጠ የነበረው ሕዝባዊ ነፃነት እና ዴሞክራሲ ወደአፎቱ ተመለሰ፡፡ ኢሕአዴግም በኢትዮጵያ ታሪክ በምርጫ ስልጣን በመልቀቅ አዲስ ምዕራፍ የመክፈት ዕድሉን በገዛ ፈቃዱ ገደለው፡፡ በርካታ አዋጆች የዴሞክራሲያችንን አቅም፣ የሕዝቡን ነፃነት እና እምነት አሽመደመዱት፡፡

ዛሬ መንግስት ዴሞክራሲን እያሳደገ እንደሆነ ቢናገርም፡፡ እስካሁን ድረስ በሕገመንግስቱ የተቀመጡት መብቶች ባይፋቁም ተግባራዊነታቸው ግን ወደ 1983 ተመልሶ ‹በ› ጉብጠት (n-curve) ሰርቷል፡፡ Continue reading

የመፈረጅ ፍራቻ እና የመፈረጅ አደጋ

አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ባሳለፍነው እሁድ (ግንቦት 12፤ 2004) ‹‹የስነጥበብ ሚና በማሕበረሰብ ውስጥ›› የሚል የውይይት መድረክ በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ውይይቱን የመሩት ፀሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበሩ አበረ አዳሙ፣ ቀራፂ በቀለ እና ሰአሊ እሸቱ ጥሩነህ ነበሩ፡፡

እነዚህ የበቁ ባለሙያዎች ጥበብ ለማሕበረሰቡ፣ ማሕበረሰቡም ለጥበብ ማበርከት ይችላሉ ያሏቸውን ጠቁመዋል፡፡ ውይይቱ የተሟሟቀው ግን ዝግጅቱ ከመጠናቀቁ አንድ ሰዓት በፊት ታዳሚዎች ጥያቄዎችን ማንሳት ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡

በውይይቱ ውስጥ አከራካሪ የነበረው ነጥብ የኪነጥበብ ሰዎች ሐሳባቸውን ለመግለፅ የመፍራት ጉዳይ ነበር፡፡ እኔም ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ መንስኤ የሆነኝ ይኸው የፍራቻ ጉዳይ ነው፡፡

ፀሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በሙያቸው የተካኑ መሆናቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሁንና በውይይቱ መክፈቻ ላይ የያዙትን ጽሁፍ ማቅረብ ከመጀመራቸው በፊት ግልፅ ማድረግ የሚፈልጉት ነገር እንዳለ ተናገሩ፡፡ ‹‹እኔ የማንም ወገንተኛ አለመሆኔን ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ፤›› አሉ፡፡ በንግግራቸው መሃልም ኪነጥበብ የማሕበረሰብ ሃያሲ ነች ካሉ በኋላ ‹‹ፖለቲካ ውስጥ አታስገቡኝ እንጂ ፖለቲካም ሃያሲ አለው›› አሉ፡፡ Continue reading

የጋንዲ፣ ኪንግ እና ማንዴላ መንፈስ

ማሕተመ ጋንዲን፣ ማርቲን ሉተር ኪንግን እና ኔልሰን ማንዴላን ስታስታውሱ መጀመሪያ ወደአዕምሯችሁ የሚመጣው ነፃነት ነው፤ በትግል የተገኘ ነፃነት፡፡ ሦስቱም ስለነፃነት የኖሩ፣ ዘመን የሞገታቸው ነገር ግን የታገሉለትን ነፃነት እየኖረ ያለው እነርሱን ተከትሎ የመጣው ትውልድ በልቡ ሃውልት ያቆመላቸው የ20ኛው ክፍለዘመን ድንቅ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሦስቱም የተወሰደባቸውን ነፃነት ለማስመለስ ብረት ማነገብ ያላስፈለጋቸው፣ ሰላማዊ የነፃነት እና የእኩልነት ታጋዮች ነበሩ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያኖችስ ከነእዚህ የዓለም ሃብቶች አንፃር ራሳችንን አይተነው እናውቅ ይሆን?

ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር እና ኔልሰን ማንዴላ የማሕተመ ጋንዲ የመንፈስ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም በማሕተመ ጋንዲ የትግል መርሕ የተቀረጹ ናቸው፡፡ የማሕተመ ጋንዲ መርሕ ‹ሰላማዊ ተቃውሞ› ነው፡፡

ማሕተመ ጋንዲ በእንግሊዞች የበላይነት የምትመራውን ሃገራቸውን – ሕንድ ነፃ ለማውጣት ይጠቀሙበት የነበረው ዘዴ – ብረት አልባ ጦርነት ነበር፡፡ ሰላማዊ እምቢተኝነት እና አለመተባበር የተባሉ መሳሪያዎች፡፡ ማሕተመ ጋንዲ በሕንድ ለሕንዳውያን እኩልነት መታገል ከመጀመራቸው በፊት በደቡብ አፍሪካ ያሉ ሕንዳውያን የሚደርስባቸውን ጭቆና በመታገል ነው የጀመሩት፡፡ ጋንዲ በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው አንደኛ መደብ ዜጋ ለሚባሉት (ነጮች) ብቻ በተፈቀደ ባቡር ውስጥ በገዛ ፈቃዳቸው (በእምቢተኝት) በመሳፈራቸው በጥበቃ ኃይሎች ተወርውረው ከባቡሩ እንዲወጡ ተደርገው ነበር፡፡ ጋንዲን ይሄ ‹‹አርፈው እንዲቀመጡ›› አላደረጋቸውም፤ እንዲያውም በእምቢተኝነታቸው በመቀጠላቸው በማግስቱ በአንደኛ መደብ የባቡር ክፍል ውስጥ መሳፈር እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ Continue reading

ደጉ ኢትዮጵያዊ፤ ከልብ ካለቀሱ እምባ እንደማይገድ ያስመሰከረ ስብስብ

“አለቀለት ሲባል ፍቅር ተሙዋጠጠ
የፌስ ቡክ ዝምድና ነገርን ለወጠ::” ~ Bizu Hiwot

“ፌስን ቡክ አድርገው የተቀጣጠሩ
በልብ መነጽር ገጹን ያነበቡ
ሸበሌ ከትመው ታሪክ አስከተቡ፡፡” ~ Desu Aragaw

እነዚህ ግጥሞች የተገጠሙት ‹ደጉ ኢትዮጵያዊ› ላዘጋጀው የዓለም ደቻሳ ቤተሰብ ገቢ ማሰባሰቢያ የስነጽሁፍ ምሽት ለተገኘው የመጀመሪያ ስኬት፣ በፌስቡክ ላይ ነው፡፡ ወደስኬቱ በኋላ ላይ የምንመለስበት ቢሆንም መጀመሪያ ‹ደጉ ኢትዮጵያዊ› ምንድን ነው፣ ማነው፣ ከየት ነው፣ ወዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች በአጭሩ እንመልስ፡፡

‹ደጉ ኢትዮጵያዊ› ከዚህ በፊት በአካል የማይተዋወቁ 16 የፌስቡክ ጓደኛሞች የፈጠሩት የፌስቡክ ቡድን ነው፡፡ የደጉ ሳምራዊን ታሪክ መነሻ አድርጎ÷ በሊባኖስ መንገድ ላይ እየተጎተተች መኪና ውስጥ እንደትገባ ከተደረገች በኋላ በማግስቱ ራሷን አጥፍታለች የተባለችውን ዓለም ደቻሳ ቤተሰቦች የእዝን ለመስጠት እና እግረ መንገዱንም ስለጉዳዩ አሳሳቢነት አነስተኛ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ለማዘጋጀት የተመሰረተው ‹ደጉ ኢትዮጵያዊ› ምንም እንኳን ሕጋዊ ሰውነት የሌለው ቡድን ቢሆንም በበጎ ፈቃደኝነት መስራት የሚፈልጉትን መስራቾቹን እና በፌስቡክ በተከፈተው የቡድኑ ገጽ ውስጥ በገቡ ከ4,000 በላይ አባላቶቹ ድጋፍ የሚከተሉትን ዓላማዎች ግብ አድርጎ ለመንቀሳቀስ ሕልም አለው፡፡ Continue reading

እስኪ እንጠያየቅ፤ አገራችን የት ነው? (መጠባበቂያ ካስፈለገ)

ከመቶ ዓመት በፊት፣ በሃገራችን ሸንጎዎች የሚካሔዱት በተጻፈ ሕግ ሳይሆን በዳኞቹ የብልሐት ፍርድ ነበር፡፡ በምኒልክ ዘመን በዳኝነት ጥበባቸው ስማቸው ደጋግሞ የሚነሱት ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ካልተሳሳትኩ – ከዳኝነት ባንዱ የሚከተለው የገጠማቸውም እርሳቸው ናቸው፤ አንድ ሕፃን ልጅ ‹የኔ ነው፣ የኔ ነው› በሚል የተካሰሱ ሁለት ሴቶች ፍርዳቸውን ሽተው ቀረቡ፡፡

ኃብተጊዮርጊስ በጣም ተጨንቀው፣ አውጥተው፣ አውርደው ውሳኔያቸውን አሳለፉ፡፡ “እንግዲህ ሁለታችሁም እናት ነኝ ብላችኋል፡፡ ሁለታችሁም እናት መሆናችሁን ምስክር አቅርባችሁ አረጋግጣችኋል፡፡ እኔም ሁለታችሁም እናት መሆናችሁን አምኛለሁ፡፡ ስለዚህ ልጁ ለሁለት ተሰንጥቆ እኩል፣ እኩል እንድትካፈሉት ፈርጃለሁ፤” ብለው ወሰኑ፡፡

ውሳኔው እንደተላለፈ፣ አንደኛዋ ሴት ብትስማማም ሌላኛዋ ግን “በቃ ይቅርብኝ፣ ልጄ አይደለም፤ ትውሰደው” አለች፡፡ ይሄን ጊዜ ኃብተጊዮርጊስ “ልጁን ለመካፈል የተስማማችውን ሴት እንድትቀጣ ፈርደው ሲያበቁ፣ በልጇ መጨከን አቅቷት ‹ልጄ አይደለም› ለማለት ለበቃችው ሴት የእናትነት መብቷን አጎናጽፈዋታል፡፡

ከመቶ ዓመት በኋላስ? Continue reading

መራመድና ባሉበት መሽከርከር፤ ሁለት የኑሮ ፈሊጦች

ወ/ሮ ሙሉ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ማሕበራትና ሴክቶራል አሶሲየሽን ፕሬዚዳንት – ልምዳቸውን እያጋሩ ነው፡፡ “ጣጣ” በማያውቀው አማርኛቸው የተራመዱበትን የሕይወት መንገድ (ልበለው ስኬት) ያወራሉ፣ ያወራሉ፤ እኔም አዳምጣለሁ፣ አዳምጣለሁ፡፡ በመሃል ‘ከራስ ጋር መወዳደር’ ስለሚባል ነገር አነሱና ተናገሩ፡፡ “መወዳደር ያለብን ከሰዎች ጋር ሳይሆን ከራሳችን ጋር ነው፣ እከሌ እንዲህ ስለሆነ እኔም መሆን አለብኝ ማለት የለብንም” አሉ፡፡ ተቀየምኳቸውና እርሳቸው ጨርሰው ታዳሚው ጥያቄ እንዲጠይቅ ዕድል ሲሰጠው እጄን ዘለግ አድርጌ አወጣሁ፡፡

“አነጋገርሽን ወድጄልሻለሁ፤” ብዬ ጀመርኩ፡፡ በነገራችን ላይ ወይዘሮዋ፣ የአራት ልጆች እናት ቢሆኑም፣ የ33 ዓመት የሥራ ልምድ ቢኖራቸውም ዕድሜያቸውን 24 እያሉ ነው የሚናገሩት (energetic መሆናቸውን ለመግለፅ ይመስለኛል፤) እንዲያውም የ24 ዓመት ሰው እንዴት 33 ዓመት የሥራ ልምድ ይኖረዋል ሲባሉ÷ ቀሪው ‘over time’ የሰራሁት ነው ብለው መመለሳቸውን ነግረውናል፡፡ ለዚያ ነው እኔም አዳራሹ ውስጥ አንቺ ማለቴ፡፡ ስቀጥል፤ Continue reading

እውትም ‘ሰሚ ያጡ ድምፆች!’

መጀመሪያ እንዲህ ነበር፤

“የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ፣

አገባሽ አስተማሪ፡፡”

ከዚያ በኋላ፤

(በጓደኛዬ እርዳታ ርዕሱን ያስታወስኩት የዶ/ር በፍቃዱ ‹ሰሚ ያጡ ድምፆች› ላይ እንደሰፈረው)

መምህራን በየክፍለሃገራቱ ተሰማርተው የነበረ ቢሆንም ደሞዛቸው 202 ብር (ቱኦቱ) ብቻ ነበር፡፡ መምህራኑ ይቺን ‹ቱኦቱ› ምን ከምን እንደምን እንደሚያደርጓት ይቸግራቸው ነበር፡፡ ስለዚህ እንደመፍትሔ ሌላ መምህርት በማግባት ወጪን በመጋራት ገቢን 404 ብር (ፎር-ኦ-ፎር) ለማደረስ ይጥሩ ነበር፡፡ (ትዳር ትርጉሙ ገቢን ማሳደግ ወይም ወጪን መጋራት እንጂ ፍቅር አልነበረም ማለት ነው፡፡) ይሄ ነገር እየተለመደ ሲመጣ የመምህር ሚስት መምህርት (ወይም የመምህርት ሚስት መምህር) ‹ፎሮፎር› የሚል ቅፅል ተሰጣቸው፡፡ “ፎሮፎሬን ተዋወቃት” ማለት ልክ “ባለቤቴን ተዋወቃት” እንደማለት ሆነ፡፡

ትንሽ ከረምረም ሲል ደግሞ፤ Continue reading